Tuesday, June 10, 2014

ልማት ያለነፃነት በቂ ነውን? ከግርማ ደርብ

ልማት ያለነፃነት በቂ ነውን? ይህችን ቀለል ያለች አስተያየት ለመረዳት እንደ መነሻ ሁላችንም ባንስማማቸውም ሁለት ነጥቦችን 'ይሁን ብለን' ብንጀምር ዋናውን ነጥቤን ታገኙልኛላችሁ ብዬ አስባለሁ። ይሁንታዎቼ የሚከተሉት ናቸው። (1) በኢትዮጵያችን እድገት ወይም እድገት የሚመስል ነገር አለ። ይህ ማለት ግን ህብረተሰቡ ከዕድገቱ ተጠቃሚ ነው ማለቴ አይደለም። (2) በኢትዮጵያችን ዴሞክራሲ፣ ነፃነትና የመሳሰሉት የክፍለ ዘመናችን መገለጫችን ፈፅመው የሉም። እነዚህ ይሁንታዎቼ እያንዳንዳቸው እንደ አንድ ርዕስ ሊፃፍባቸው ይገባ ነበር ግን የእኔ ነጥቦች እነርሱ አይደሉም። በዚህች አጭር አስተያዬቴ ላወራ የፈለኩት "ነፃነት ባይኖር እድገት እንካለ ድረስ በቂ ነው ወይ?" የሚል ነው። በመጀመሪያ ግን ሰሞኑን የወጣ አንድ ጥናት - ዴሞክራሲ እድገገትን ያፋጥናል የሚል መደምድመሚያ ላይ ደርሷል። እዚህ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የብዙ አገሮችን የ60 ዓመት ዳታ ተጠቅመዋል። በዚህ ጥናትም "ቆንጆ አሳቢ፣ ለሕዝቡ ተቆርቋሪ መሪዎች ላላደጉ አገሮች ከዴሞክራሲ ይልቅ ለልማታቸው ይበጃቸዋል" የሚለውን የቆየ እና አንዳንድ የቻይናን እድገት ለመተንተት የሚጠቀሙትን ትንታኔ ተችቷል በማስረጃም አስደግፎ ውድቅ ለማድረግ ሞክሯል። ቁም ነገሩ ግን ዴሞክራሲ ለልማት በጀም አልበጀም ለልማት ብለን የምንተወው ነገር ነው ወይ። የአገሬ ሕዝብ ጠግቦ እያደረ እንዳልሆነና በኑሮ ውድነት እየተጠበሰ ለመሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ቢሆንም - ያ እንኳን ቢሆን ያለ ነፃነት መኖር ይቻላል ወይ? በተለይ በ21ኛው ክፍለዘመን። ልማቱ እንኳን ቢኖር (እንዳልኳችሁ ይህ በራሱ አወዛጋቢ ነው) ያለ ነፃነት እንዴት ይኖራል። ነፃነት የለም ስል ምን ማለቴ ነው፧ ነፃነት አለመኖሩ በምን ሊገለጽ ይችላል፧ የሚከተሉትን ጥቂትነጥቦች ላንሳ: 1. የኦሮሞ ተማሪዎች ግድያ በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ባለመስማማታቸው ምክኒያት ባዶ እጃቸውን ሰልፍ የወጡ ተማሪዎችን ተገድለዋል። ይህ ማለት እኮ በአገርህ ላይ በሚደረገው ነገር ተስማማህም አልተስማማህም በምንም አይነት መንገድ እንደዜጋ አስተያየት ሊኖርህ አይችልም ማለት ነው። ከመንግንግስት ዕቅድ ጋር አለመስማማት እና ተቃውሞህን በሰላማዊ መንገድ መግለፅ ያስገድላል። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ተሳክቶልህ "ምን ልብላ ምን ልልበስ" ብለህ ሳትጨነቅ ብትኖር እንኳን በአካባቢህ በሚደረጉት ነገሮች ላይ ምንም አይነት አስተያየት ሳይኖርህ መኖር ከእንስሳ ኑሮ የሚሻል አይመስለኝም። ልማት ወይም እድገት "የምን ልብላና የምን ልልበስን" ጥያቄ ሊመልስ ይችላል። ነገር ግን እንደሰው ተሰሚነት ኖሮህ በነፃነት አስተያየትህን ሰጥተህ እንድትኖር አያስችልህም። ይህ ከቶ በቂ ሊሆን ይችላል ወይ? ከኦሮሞ ተማሪዎች ግድያ በላይ ነፃነትአለመኖርን ምንስ ሊገልፀው ይችላል።
2. መንግስት ባፀደቃቸው የተቃውሞ ሰልፎች ላይ መሳተፍ እየተሰልልክ እና እየፈራህ እንድትኖር ያደርግሃል። ተቃዋሚ ፓርቲዎች መንግስትን አስፈቅደው በጠሩት ሰልፍ ላይ ስለተሳተፉ ብቻ ተራ እና ምንም ጉዳት የማያደርሱ በሃሳቡ ስለተስማሙ ብቻ ሰልፍ ላይ የወጡ ዜጎች ላይ የሚደርሰው ስለላ እና ዛቻ በጣም አስገራሚ ነው። በአዲስ አበባ፣ በጎንደር፣ በባሕር ዳር፣ በድሬ፣ በደሴ እና በሌሎችም ከተሞች ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጠሩት ሰልፍ ላይ የተሳተፉ ዜጎች ላይ የደረሱት ሰቆቃዎች የማይታመኑ ናቸው። ስንቶች ታሰሩ። የሚታወቁ ሰወች ሲታሰሩ ባንድም በሌላም መንገድ ለሕዝቡ እና አኢንተርናሽናል ማሕበረሰቡ ይደርሳል። ግን የማይታወቁ ሰወች ሲታሰሩ እና ሲሰቃዪ ማንም አያይላቸውም። ስንቶች እስር ቤት ይማቅቃሉ። ስንቶችስ ደግሞ አሁን ምን ይመጣብኝ ይሆን በማለት እየተሳቀቁ ይኖራሉ። በልማቱ ተጠቃሚ ሆነህ፣ ተሳክቶልህ በኢኮኖሚህ ጥሩ ሆነህ፣ ፍላጎትህን ብታሟላ እንኳን ሃሳብህን በሰላማዊ መንገድ ሳትገልፅ መኖር በቂ ነው ወይ? ሌላው ቢቀር መንግስት በፈቀዳቸው ሰላማዊ ሰልፎች ላይ መሳተፍ እንዴት እስደወንጀለኛ ሲያሰልል ያኖራል። ከዚህ በላይ ምን ነፃለት አለመኖርን ምን ሊገልፀው ይችላል። 3. ቤትህንና ኑሮህን የሚቀይር የመንግስት ፖሊሲ ለውጦች ላይ ምንም አይነት የተቃውሞ ቃል ትንፍሽ ማለት ውድ ህይወትህን ሊያሳጣህ ይችላል። መንግስት ከተሞችን ዘመናዊ ለማድረግ የሚያወጣቸው እቅዶች ብዙዎችን ከኖሩበት ቦታ አፈናቅሏል፥ የብዙዎችንም ቤት አፍርሷል። የከተሞቻችንን እቅድ ብዙዎቻችን ብንደግፍም ሰፈር እንዲቀይሩ የሚገደዱትንና ቤቶቻቸው እንዲፈርስ የተወሰነባቸው ሰዎች የሚያልፉበትን መከራ እንገነዘባለን። እነዚህ ሰዎች ከከተማ እቅድ አስፈፃሚዎች ጋር ቢጋጩ አይፈረድባቸውም። ማንም የሚረዳው የታወቀ የመከራ ጊዜ ነው - ለእነርሱ። ከጥቂት ወራት በፊት በባህር ዳር ከተማ የሚከተለው ተፈፅሟል። ቤታችንን ያለምንም ካሳ አታፈርሱብንም በማለት በተከራከሩና አናስፈርስም ባሉ ወደ ሶስት የሚሆኑ የከተማው ነዋሪዎች በአደባባይ በጥይት ተደብድበው እንደሞቱ ተደግረዋል። አሁንም ጥያቄዬ - በልማቱ ተጠቃሚ ሆነህ፣ ተሳክቶልህ በኢኮኖሚህ ጥሩ ሆነህ፣ ፍላጎትህን ብታሟላ እንኳን ተቃውሞህን በሰላማዊ መንገድ ሳትገልፅ መኖር በቂ ነው ወይ? ከኖርህበት ቦታ ስትፈናቀልና ቤትህ ሲፈርስ እንኳን መቃወም አትችልም? እንደሚታረግ እንደፋሲካ በግ አንዲት ቃል ሳትተነፍስ ብቻ ነው መኖር ያለብህ? ሌሎችንም ብዙ መጥቀስ ይቻላል። እጅግ ብዙ አሰቃቂ ከሕዝብ ጆሮ ያልደረሱ ግፎችም እንደደረሱ እርግጠኛ ነኝ። እርስዎም ይህችን አጭር አስተያየት ሲያነቧት "በእኔስ ይህ ደርሶ የለም እንዴ - ሕዝብ አልሰማውም እንጂ" የሚሉት እንዳለ እርግጠኛ ነኝ። እናም ዋናው ነጥቤ ወደ ርዕሴ ይመልስዎታል። ልማት ያለነፃነት በቂ ነውን? በልማቱ ተጠቃሚ ሆነው፣ ተሳክቶልዎ ኢኮኖሚዎ ጥሩ ሆኖ፣ ፍላጎትዎን ቢያሟሉ እንኳን ተቃውሞዎን በሰላማዊ መንገድ ሳይገልፁ መኖር በቂ ነው ወይ? ሃሳብዎ ከመንግንት ጋር የማይስማማ ከሆነ አንዲት ቃል ትንፍሽ ሳይሉ እንደሚታረድ በግ ዝም ብለው ወደዱም አልወደዱም መንግስት ያለውን ብቻና ብቻ እንደ እግዚአብሔር ቃል እየተቀበሉ ያለ ቅንጣት የነፃነት ሽራፊ መኖር በቂ ነውን???

ቸር ይግጠመን።

No comments:

Post a Comment