Saturday, June 14, 2014

ፊንፊኔን ውሃ በላት ብላችሁስ (ሄኖክ የሺጥላ ) " .....ታላቁ ገጣሚ ሰለሞን ደሬሳ ” ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልዶ እኔ የጠራሁ አማራ ወይም የጠራሁ ኦሮሞ ነኝ ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር አላዋቂነት ይመስለኛል ; እስኪ ስንቶቻችን ነን በሴት አያቶቻችን በር ማን እንዳለፈ በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው?" ብሎ ነበር።"

ፊንፊኔን ውሃ በላት ብላችሁስ (ሄኖክ የሺጥላ )

ፊንፊኔን ውሃ በላት ብላችሁስ ? የምን ውሃ የቡልቡላ ወይስ የአባ ሳሙኤል እንዳትሉኝ። አይደለም  ፊንፊኔን የበላት ውሃ ፣ ውሃ የማይመስል የታሪክ ውሃ ነው። የ ምንነት ጎርፍ። ባንድ ሌሊት እጥብ አርጎዋት አደረ።
ነገሩ እንዲህ ነው  ሰሞኑን አዲስ አበባ ውስጥ አንድ ጥንታዊ ቤተ መንግስት ተገኘ አሉ ፣ እና ገረመኝ ። ከዛ በቃ ዝም አልኩ ፣ እንዲያው ዝም ነው ዝም ዝም ነው ያለው አባት ዓለም ጸጋዬ ገ/ምድህን።
እናላችሁ ታላቁ ገጣሚ ሰለሞን ደሬሳ  ” ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልዶ እኔ የጠራሁ አማራ ወይም የጠራሁ ኦሮሞ ነኝ ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር አላዋቂነት ይመስለኛል ; እስኪ ስንቶቻችን ነን በሴት አያቶቻችን በር ማን እንዳለፈ በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ፣ የኔን  ንጹ ኦሮሞነት የሚያውቁት የሴት አያቴ ብቻ ናቸው”  ብሎ ነበር ።  ጋሼ ሰለሞን እንዳንተ አይነት በምኒሊክ ጊዜ እንጂ በ ወያኔ ጊዜ አልተፈጠሩም ፣ አሁንም እድሜውን ያብዛልህ።  እና ይቺን አባባል  ለ ፊንፊኔ በዋሳትስ ” የኢትዮጵያ ምድር ሆኖ እኔ የትግራይ መሬት ነኝ ፣ እኔ የ ኦሮሞ መሬት ነኝ ብሎ ማለት አላዋቂነት ይመስለኛል ፣ እስኪ ስንቶቻችን ነን ፣ በማን በሬ እንደታረስን ፣ በማን እጅ እንደለሰለስን፣ በማን ደም እንደጸናን፣ በማን እግር እንደቀናን   በእርግጠኝነት የምናውቀው ፣ አረ ስንቶቻችን ነን ፣ ከባድማነት ወደ ለምነት ፣ ከ አረም፣ ከኩይሳ እና ከ ሰንሰል ቤትነት ወደ ነጭ ጤፍ አውድማነት በማን ክንድ እንደተቀየርን የምናውቅ ፣ አረ ስንቶቻችን ነን ፣ ለባዕድ መታረስ ፣ በባዕድ መታፈስን እምቢ ያሉ እግሮች የተሸከምን ፣ ስንቶቻችን ነን በምሬት እና ምሪት መሬት የሆንን? ስንቶቻችን ነን የክልል ሳይሆን የህዝብ አፈር የሆንን ፣ ስንቶቻችን ነን የዘውግ ወይም የዘር ሳይሆን የ ፍጥረት ማደሪያ የሆንን  ብሎ የሚጠይቅ አይመስላችሁም ?
ለማንኛውም የ ንጉስ ዳዊት ቤተሰቦች ካላችሁ ወጣ ወጣ በሉ ። እኔ ግን ከአሁን በሁዋላ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ነች የሚለው ሃሳብ ላይ ማክረር እጀምራለሁ ። የሚቃወም ካለ በምርጫ ያድርገው ። ነጮች እንድንከባበር ሳይሆን እንድንደነባበር በሰልንሩልን የእኩልነት  ምርጫ ፣ እንድንፋቀር ሳይሆን ” የራስን  ዕድል በራስ መወሰን ” በሚል አባዜ እንድንወለካከፍ ፣ ከፍ እንድንል ሳይሆን በፈለጉ ጊዜ እንደ ድመት “ክፍ” ሊሉን የሚያስችላቸውን ጥንካሬ ይሰጣቸው ዘንድ ስለሰሩልን እና ስላሴሩል  ዴሞክራሲ ፣ ምርጫ ብለው ስለጠሩት እና በፍቃዳቸው ስላጠሩት ማንታችን ፣ ይሄ ስለ ሕዝብ  እኩልነት ሳይሆን ስለ አእምሮ ስንኩልነታችን ሲባል እንድንጠፋበት ዘንድ ራሳችን ራሳችን ላይ እንደ እባጭ ማፈንጃ ስብ ቀብተን ስለጠመምነው ድንቁርናችን ፣ ስለ እሱና በሱ ፣ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ አካል ነች ፣ አይደለችም ብለን እናውጅ ። አዋ በ ሪፈረንደም ። አዋ ኤርትራ  እንኩዋ የሄደችው በሱ አይደል ፣ እንደሱዋማ ሃሳብ ቢሆን ዛሬ ወርቅ ትፈትል  ነበር ፣ አሱዋም አልገባትም ፣ ከሱዋ ማጥ ያልተማሩትም አልገባቸውም ። መገንጠል ነጻ ያወጣ ይመስል ፣ ሰው ከጉንዳን ባነሰ ሁኔታ ሲያስብ ፣ ሰው ያንበጣን  ያህል እንኩዋ አንድነት ሲፈራ፣ እንዲህ የተቀበረ ቤተመንግስት ልፈፋውን ሁሉ ካ-ዘቦትነት በፍጥነት ወደ ሰርክነት ሲቀይረው ፣ በእውነት ማነን እላለሁ ።  ያንተ ሀገር በዲዮጋን ተረት አላረሰችም ፣ የማርክስ ፍልስፍና ላንተ ምድር ደም እንጂ ትራክተር አላበረከተም ፣ የ አማሪካኖች ስልጣኔ አንተን ምኞታም እንጂ ታታሪ አላደረገህም ፣ ያንተ ያልሆነ አንተን አይፈጥርም ፣ ያንተ ባልሆነ ታሪክ ብትሰራ እንኩዋ አንተ አይደለህም ።
እና ሃሳቤን ስቀጥል ፣  ፊንፊኔን ውሃ በላት ፣ ባይበላት እንኩዋ ተፍቶዋታል ፣ ሌላውም እንደዚያ ፣ ደሞ ነገ መንዝ ውስጥ የ ትግሬ ንጉስ ቤተ መንግስት ይገኝ ይሆናል ፣ አፋር ውስጥ የ ወላይታ ውጭት ፣ ሱማሌ ውስጥ የ ኦሮሞ ፈረስ፣ ትግራይ ውስጥ የ መንዝ አገልግል ። እና ማነን እኛ አፋችንን ሞልተን የጠራን ከላይ ፣ የጠራን ወሳኝ ፣ የጠራን ድንበርተኛ የሆነው ። እስኪ ደሞ ሌላ የሚያስተሳስር ፣ ሌላ የሚያዛምድ ፣ ሌላ ከ ብሔር ባላባት እና ባለቤትነት ወደ ሕዝብ መሪነት እና ውህደት የሚመራ ቤተ መቅደስ ወሎ ውስጥ ይገኝ ፣ እስኪ ደሞ ትግራይ ውስጥ የ የጁ ጦር ፣ አምቦ ውስጥ የ ጎንደር ወጭት ተቆፍሮ ይገኝ ። እደግመዋለሁ ጅማ ውስጥ የ አባ ጅፋር የባሪያ ማጎሪያ ሳይሆን የ ሃብተ ጊዮርጊስ ዝናር ይገኝ ፣ አምቦ ውስጥ የኦነግ ጥንስስ ሳይሆን  የጸጋዬ መድብል ይገኝ ፣ ትግራይ ውስጥ የ መለስ እና የመሰሎቹ ዘረኝነት ሳይሆን የአሉላ ጠብ መንጃ ይገኝ ።
እኛ  እ እ እ  እኛን ለታሪክና  ለሞታችን ትቼ ፣ እዝህ ጋ አቆማለሁ ።

1 comment:

  1. You are illiterate professor like same Mesfin weldemariam dear ! Try to identify what you know and not before leaving your hatred sympathy !

    ReplyDelete