በአሃራማያ ዩኒቨርስቲ በተጣለ ቦንብ አደጋ ደረሰ
(ኢ.ኤም.ኤፍ) – በኦሮሚያ ከፍተኛ ተቋማት ውስጥ የተጀመረው ረብሻ ወደ ከተሞች እየተዘመተ መሆኑን ዛሬ ምሽት ያገኘነው መረጃ አሳውቋል። የአምቦ ዩኒቨርስቲ ረብሻ ወደ ከተማው ተዛምቶ ሰባት ሰዎች ተገድለዋል። በመዳ ወላቡም ከዩኒቨርስቲው አልፎ በከተማው በተነሳ ረብሻ ሶስት ሰዎች ሞተዋል። ዛሬ ቀን ላይ ደግሞ በሃረማያ ዩኒቨርስቲ ኳስ ጨዋታ ይመለከቱ የነበሩ ከመቶ በላይ ተማሪዎች ላይ ቦንብ ተጥሎባቸው፤ ሰባ ያህሉ ላይ የመቁሰል አደጋ ሲደርስ አንድ ተማሪ ሞቷል። በጅማ እና በሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ከኦሮሞ ተማሪዎች ጋር ያልተባረሩ ወይም የሌላ ክልል ተወላጆች ላይ ትንኮሳ እና ድብደባ እየተፈጸመባቸው ነው። “ኦሮሚያ ለኦሮሞ” የሚል መፈክር ይዞ የሚንቀሳቀሰው አመጽ፤ አጀማመሩ ሰላማዊ ቢመስልም፤ በውስጡ ግን በሌላው ብሄረሰብ ላይ ጥላቻን የሚያሰፋ በመሆኑ፤ በሌላው ኢትዮጵያዊ ዘንድ ህዝባዊ ድጋፍን እየተነፈገ ነው። ይህም ሆኖ የኦህዴድ እና የህወሃት ሃይሎች በተቀናጀ መልኩ ሃሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ በሚገልጹ ተማሪዎች ላይ እየወሰዱ ያሉት የግድያ እርምጃ ብዙዎችን ቅር አሰኝቷል። በመጨረሻም “በተቃዋሚዎቹ በኩል የተነሳውን ቀላል ጥያቄ ወደ ጥላቻ የሚወስዱ አካሎችም ሆኑ የሃይል እርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ የሚሰጡ ባለስልጣናት ጉዳዩ ወደከፋ ደረጃ እንዳይሸጋገር አንድ አፍታ ቆም ብለው ሊያስቡበት ይገባል” የኢ.ኤም.ኤፍ መልዕክት ነው።
No comments:
Post a Comment